ተሸከርካሪዎችን ከጅቡቲ ወደብ ወደ ሀገር ውስጥ በማስገባት የደንበኞችን እርካታ ማሳደግ ተችሏል፤

ታህሣስ 20 ቀን 2015 ዓ.ም (ኢዲአር)፡- የኢትዮጵያ ባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አገልግሎት ድርጅት (ኢባትሎአድ) ለመጀመሪያ ጊዜ ከጅቡቲ ወደብ ወደ ሀገር ውስጥ በባቡር ያጓጓዛቸው ተሸከርካሪዎች በያዝነው ሳምንት ማክሰኞ ዕለት እንዶዴ ባቡር ጣቢያ ተራግፈው ወደ ገላን የተሽከርካሪ ጊዜያዊ ማቆያ ተርሚናል መጓጓዛቸውን ገለፀ፡፡ ድርጅቱ በይፋዊ የማህበራዊ ገፁ እንዳሰፈረው የተሸከርካሪዎቹ ደህንነት ተጠብቆ፣ በፍጥነትና በአነስተኛ ወጪ በርከት ያሉ ተሽከርካሪዎችን ወደ ሀገር ውስጥ ማስገባት መቻሉን ጠቁሟል፡፡ በተሸከርካሪ ከ3 እስከ 4 ቀን የሚፈጀውን ጉዞ በአስተማማኝ ሁኔታ በሰዓታት ውስጥ ከወደብ ወደ ሀገር ውስጥ በማስገባት ጊዜን በመቆጠብ የጉዞ ወጪን በከፍተኛ ሁኔታ መቀነስ መቻሉን አክሏል፡፡ የጭነትና የህዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት በመስጠት ለሀገራችን ኢኮኖሚያዊ እድገት ከፍተኛ ሚና በመጫወት ላይ የሚገኘው የኢትዮ ጅቡቲ ባቡር ትራንስፖርት አ.ማ በ2015 በጀት ዓመት ከጀመራቸው አዳዲስ አገልግሎቶች መካከል አንዱ ተሸከርካሪዎችን ከጅቡቲ ወደብ ወደ መሀል ሀገር የማስገባት አገልግሎት አንዱ ነው፡፡ በአንድ ጊዜ 240 ተሸከርካሪዎችን የማጓጓዝ አቅም ባላቸው የባቡር ፉርጎዎች ደህንነቱ በተጠበቀ መለኩ በፍጥነትና በተመጣጣኝ ዋጋ የማጓጓዝ አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል፡፡ የተቋማችን ደንበኛ የሆነው የኢትዮጵያ ባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አገልግሎት ባሳለፍናው ማክሰኞ ወደ ሀገር ውስጥ ያስመጣቸውን ተሸከርካሪዎች ከጅቡቲ ወደብ ወደ እንዶዴ ባቡር ጣቢያ በማምጣት ደንበኛችን ወደሚፈልገው መዳረሻ እንዲንቀሳቀሱ አድርገናል፡፡ በአገልግሎታችን ፍጥነት፣ ጥራትና ቅልጣፍና ከደንበኛችን የተሰጠን ምስክርነት የበለጠ በአገልግሎታችን እንድንበረታ የሚያደርገን በመሆኑ ምስጉንና ታታሪ ሰራተኞቻችንን ይዘን የላቀ አገልግሎት መስጠታችንን አጠናክረን እንቀጥላለን፡፡
Facebook
Twitter
LinkedIn