የባቡር መስመር ላይ ስርቆት የፈፀሙ ተጠርጣሪዎች በአራት እና ሰባት ዓመት እስር ተቀጡ.

  • Post author:
  • Post comments:0 Comments
  • Reading time:3 mins read

ጥቅምት 8 ቀን 2016 ዓ.ም (ኢዲአር)፦ በኢትዮ ጅቡቲ ባቡር ትራንስፖርት አ.ማ የባቡር መሠረተ ልማት ላይ ስርቆት የፈፀሙ አራት ተጠርጣሪዎች ጉዳያቸው በፍርድ ቤት ሲታይ ቆይቶ ተጠርጣሪዎቹ ጥፋተኛ ሆነው በመገኘታቸው የአራት እና ሰባት ዓመት እስር ተፈርዶባቸዋል።

የገላን ፖሊስ ጣቢያ በእንዶዴ አካባቢ የባቡር ሃዲድ ማቀፊያ ብሎን የሰረቁ ሁለት ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ስር በማዋልና ምርመራ በማድረግ መዝገቡን ለዐቃቤ ህግ አስረክቧል።

የሸገር ከተማ ዐቃቤ ህግ በተጠርጣሪዎች ላይ በ1996 ዓ.ም ተሻሽሎ በወጣው የወንጀል ህግ አንቀጽ 32 (1) (ሀ) እና 669 (1) (ለ) ስር ለሸገር ከተማ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ክስ አቅርቧል።

በመዝገብ ቁጥር 75879 ክስ ተመስርቶ ጉዳያቸው በህግ ሲታይ የቆየው ተከሳሾች ወንጀሉን አልፈፀምንም ብለው ተከራክረዋል።

ዐቃቤ ህግ በበኩሉ ክሱን የስረዱልኛል ያላቸውን ማስረጃዎቸና ምስክሮች በማቅረብ ውሳኔ እንዲሰጥበት ፍርድ ቤቱን ጠይቋል።

የሸገር ከተማ ፍርደ ቤት መስከረም 22 ቀን 2016 ዓ.ም በዋለው ችሎት ተከሳሾች ክሱን መከላከል ባለመቻላቸውና በቀረበባቸው ማስረጃዎችና የሰው ምስክር መሠረት ጥፋተኛ ሆነው በመገኘታቸው እያንዳንዳቸው በሰባት ዓመት እስራት እንዲቀጡ ውሳኔ አስተላልፏል።

በተመሳሳይ በሸገር ከተማ ገላን ጉዳ ክፍለ ከተማ የተያዙ የባቡር ሃዲድ ማቀፊያ ብሎን የሰረቁ ሁለት ተጠርጣሪዎች በፖሊስ ቁጥጥር ስር ውለው ምርመራ ሲደረግባቸው ቆይቶ የሸገር ከተማ ዐቃቤ ህግ በመዝገብ ቁጥር 76192 ክስ መስርቶ ጉዳዩን ሲከታተል ቆይቷል።

የሸገር ከተማ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ጥቅምት 2 ቀን 2016 ዓ.ም በዋለው ችሎት ውሳኔ አሳልፏል።

ተጠርጣሪዎቹ የቀረበባቸውን የወንጀል ክስ አልፈፀምንም ብለው የተከራከሩ ሲሆን አቃቤ ህግ ክሱን ያስረዱልኛል ያላቸውን ምስክሮች በማቅረብ ተከሳሾች ላይ ክሱን አረጋግጧል።

በዚህም መሠረት የሸገር ከተማ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ተጠርጣሪዎቹ ጥፋተኛ ሆነው በመገኘታቸው እያንዳንዳቸው በአራት ዓመት እስራት እንዲቀጡ ውሳኔ አስተላልፏል።

Leave a Reply