ጥቅምት 13 ቀን 2015 ዓ.ም (ኢዲአር)፡- የ”ቤልት ኤንድ ሮድ ፕሮጀክት” አካል የሆነው የኢትዮ ጅቡቲ ባቡር መስመር ኢትዮጵያ የወጪ ንግድ እንቅስቃሴዋን እንድታሳልጥ ከፍተኛ አስተዋፅኦ እያበረከተ እንደሚገኝ ተገልጿል፡፡
ከቀናት በፊት 10ኛ ዓመቱን ያከበረውና በቻይና ፕሬዚዳንት ሺ ጂንፒንግ አነሳሽነት ተግባራዊ በተደረገው የ”ቤልት ኤንድ ሮድ ፕሮጀክት” 3ኛው ፎረም ላይ የፕሮጀክቱ ውጤታማነትና ቀጣይ አቅጣጫዎች ላይ ውይይት ተደርጓል፡፡ ይህን መሠረት በማድረግ የቻይናው ግሎባል ቴሌቪዥን ኔትወርክ (ሲጂቲኤን) ሰፊ ዘጋባ አስነብቧል፡፡
ሲጂቲኤን በዘገባው የኢትዮ ጅቡቲ ባቡር ትራንስፖርት የኢትዮጵያን የተመረጠ ቡና እና ሌጦ ከመዲናዋ አዲስ አበባ ወደ ጅቡቲ ወደብ በማድረስ ረገድ ከፍተኛ ሚና እየተጫወተ መሆኑን ዘግቧል፡፡
የባቡር መስመሩ ከመገንባቱ በፊት ኢትዮጵያ የወጪንግዷን ከአዲስ አበባ ጅቡቲ ለማድረስ ቢያንስ ሶስት ቀናት ይወስድባት እንደነበር ያስታወሰው ሲጂቲኤን አሁን ላይ የቤልት ኤንድ ሮድ ፕሮጀክት በመተግበሩ የጭነት የመጓጓዣ ጊዜን ከ20 ሰአት ባነሰ ጊዜ እንድታደርስ ማስቻሉን አመላክቷል፡፡ የቤልት ኤንድ ሮድ ፕሮጀክት አካል የሆነው የባቡር መስመሩ የመንገደኞችና የጭነት አግልግሎት እንዲሰጥ ታስቦ መዘርጋቱን ዘገባው አስታውሷል፡፡
የባቡር መስመመሩ በኢትዮጵያ የተመረተ “Made in Ethiopia” የሚል ወጪ ንግድን በባሕር ወደ እሲያ እና አውሮፓ መላክ የሚያስችል የባቡር- ባሕር ጥምር የትራንስፖርት አገልግሎት ዕውን ማድረግ እንደሚያስችል ጠቁሟል፡፡
የኢትዮ ጅቡቲ ባቡር ትራንስፖርት አገልግሎት መጀመር ከኢንዱስትሪ ፓርኮች ግንባታ ዕውን መሆን እና ሥራ መጀመር ጋር ተጣምሮ ለኢትዮጵያ ብልፅግና ዕውን መሆን የተጀመረውን ሂደት ማገዙን ሲጂቲኤን ዘግቧል፡፡