የህብረተሰቡን ግንዛቤ በማሳደግና ቅንጅታዊ አሰራሮችን በማጠናከር በባቡር መሰረተ ልማቱ ላይ የሚያጋጥሙ ችግሮችን መቅረፍ እንደሚገባ ተጠቆመ

  • Post author:
  • Post comments:1 Comment
  • Reading time:11 mins read

ጥቅምት 15 ቀን 2016 ዓ.ም (ኢዲአር)፡- ይህ የተጠቆመው በኢትዮ ጅቡቲ ባቡር ትራንስፖርት አ.ማ እና በቢሾፍቱ ከተማ አስተዳደር ትብብር በባቡር ደህንነት ዙሪያ ከፀጥታ አካላት ጋር ምክክር በተደረገበት ወቅት ነው፡፡

የኢዲአር ቺፍ ሎጂስቲክና ግዢ ኦፊሰር እና የዋና ስራ አስፈፃሚ ተወካይ ኢንጂነር ሄኖክ ቦጋለ በዚህ ወቅት እንዳሉት የባቡር መስመሩን ደህንነት በማረጋገጥ ረገድ የፀጥታ አካላት ያላቸው ሚና ከፍተኛ በመሆኑ የሚያጋጥሙ የብሎን ስርቆቶችና የመሠረተ ልማት ጉዳቶችን ለመከላከለል እንደሁልጊዜው ሁሉ ተናበን መስራት ያስፈልጋል ብለዋል፡፡

የባቡር መስመሩ በሚያልፍባቸው ከተሞችና ከተማ አስተዳደሮች ከፀጥታ አካላት ጋር ተደጋጋሚ ውይይቶች እየተካሄደ እንደሚገኝና አበረታች ለውጦችን ማስመዝገብ መቻሉን ገልፀው በቢሾፍቱ ከተማ የተዘጋጀው ይህ የምክክር መድረክ ስኬቶችን ለማስቀጠል የሚረዳ ነው ብለዋል፡፡

የኢዲአር ስትራቴጂክና ፓርትነርሺፕ ቡድን መሪ አቶ ያዕቆብ ካርቱ እያጋጠሙ ያሉ የደህንነት ችግሮችና በጥናት የተለዩ ክፍተቶችን ጨምሮ እየተወሰዱ ያሉ እርምጃዎችን በተመለከተ ሰፊ ገለፃ ሰጥተዋል፡፡

አቶ ያዕቆብ በገለፃቸው እንዳሉት ከፀጥታ አካላት ጋር በመቀናጀት በተወሰዱ እርምጃዎች ችግሮችን መቀነስ ቢቻልም በቢሾፍቱ ከተማ አስተዳር የባቡር መስመር ውስጥ አሁንም ድረስ የብሎን ስርቆትና የመሰረተ ልማት ውድመት እያጋጠመ ይገኛል ብለዋል፡፡

ከቢሾፍቱ ከተማ አስተዳደር የመጡ የፀጥታ አካላት የመስመሩን ደህንነት ለማረጋገጥ እየተሰሩ ያሉ ጅምር ስራዎች አበረታች መሆናቸውን በመግለፅ የተጠቀሱት ክፍተቶችን ላይ በትኩረት ሊሰራ እንደሚገባ አስተያየት ሰጥተዋል፡፡

የህብረተሱን ግንዛቤ ማሳደግና ወንጀሎችን አስቀድሞ መከላከል ላይ ይበልጥ መስራት እንደሚገባ የጠቆሙት የውይይቱ ተሳታፊዎች የፖለቲካ አመራሩ የላቀ ሚና መጫወት እንደሚገባው፣ ቅንጅታዊ አሰራሮችን ማጠናከር፣ ተጠርጣሪዎች ላይ አስተማሪ እርምጃ መውሰድ፣ የፀጥታ አካላት በጥብቅ ዲስፕሊን የጀመሩትን የቁጥጥር ስራ ይበልጥ ማሳደግና ለቁጥጥር ስራው አስፈላጊ የሆኑ ግብዓቶችን ማሟላት እንደሚገባ አክለዋል፡፡

በቀረቡት አስተያየቶች ዙሪያ የኢዲአር ቺፍ ሎጂስቲክስና ግዢ ኦፊሰር ኢንጂነር ሄኖክ ቦጋለ፣ የኦሮሚያ ትራንስፖርት ኤጀንሲ ሃላፊ አቶ ጀማል ከድር እና የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ተወካይ ኮሚሽነር ዲባባ ረጋሣ ምላሽና ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡

በምክክር መድረኩ የትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር የባቡር ዴስክ ዘርፍ ሃላፊ ወ/ሮ ኤደን ግርማ፣ የኢዲአር ከፍተኛ አመራሮችን፣ የፌዴራል ፖሊስ የባቡር ዲቪዥን አባላት፣ የቢሾፍቱ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ተወካይ፣ የቢሾፍቱ ከተማ ፖሊስ መምሪያ የስራ ሃላፊዎችና ከወረዳና ዞን የመጡ የፀጥታ ሃላፊዎች ተሳታፊ ሆነዋል፡፡

This Post Has One Comment

  1. jemal

Leave a Reply