ጥቅምት 24 ቀን 2016 ዓ.ም (ኢዲአር):- በኢትዮ-ጅቡቲ ባቡር ትራንስፖርት አ.ማ አሰሪነት በአማሮ ዞን ኬሌ ከተማ ሲከናወን የቆየው የመቄሬዲ አፀደ-ህፃናት ት/ቤት ግንባታ ተጠናቀቀ።
የዞኑ ከፍተኛ አመራሮችና የኢዲአር ቴክኒካል ኮሚቴ አባላት በተገኙበት የግንባታ ሂደቱ መጠናቀቅን አስመልክት በት/ቤቱ ቅጥር ጊቢ ምልከታ ተደርጓል።
የኢዲአር የሴፍቲ፣ኢንቫሮመንትና ኳሊቲ ዲፖርትመንት የኢንቫሮመንት ቡድን መሪ ኢንጂነር ገመቹ አለማየሁ በዚህ ወቅት እንደተናገሩት ኢዲአር የባቡር መስመሩ በሚያቋርጣቸው ክልሎችና ከተማ አስተዳድሮች ለሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎች ከሚያደርገው የማህበራዊ አገልግሎት በተጨማሪ በሀገራዊ የበጎ ስራ ተግባር ላይ የላቀ ተሳትፎ እያደረገ እንደሚገኝ ጠቁመው የመቄሬዲ አፀደ-ህፃናት ት/ቤት ግንባታም የዚሁ ሀገራዊ የበጎ ስራ አካል ነው ብለዋል።
ኢንጂነር ገመቹ በግንባታ ሂደቱ የዞኑ አመራሮች ላደረጉት ድጋፍ በኢዲአር ማኔጅመንትና በቴክኒክ ኮሚቴው ስም አመስግነዋል።
የዞኑ ኮንስትራክሽንና ከተማ ልማት መምሪያ ዋና ሃላፊ አቶ ዮሐንስ ሀይሌ በበኩላቸው ት/ቤቱ በአጭር ጊዜ ግንባታው ተጠናቆ ለአገልግሎት ዝግጁ መሆኑ እንዳስደሰታቸው ገልፀው የኢዲአር ማኔጅመንትና የግንባታው ቴክኒክ ኮሚቴ ላበረከቱት የላቀ አስተዋፅኦ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
በጉብኝቱ የዞኑ ባህልና ቱሪዝም መምሪያ ሃላፊና የዞኑ አስተዳደር ተወካይ አቶ አባየሁ በቀለ፣ የዞኑ ብልፅግና ቅርንጫፍ ፅ/ቤት የፖለቲካና ርዕዮተዓለም ሃላፊ አቶ ብርቅነህ ጌታሁን፣የዞኑ ብልፅግና ቅርንጫፍ ፅ/ቤት የፓለቲካ አደረጃጀት ዘርፍ ሃላፊ አዳሙ አንኬላ፣የዞኑ የኮንስትራክሽን መምሪያ ሃላፊ አቶ ቻላቸው አባተ እና የዞኑ ት/ት መምሪያ ሃላፊ አቶ ሰረበ አሻግሬ ተገኝተዋል።
በቀጣይ ኢዲአር የትራንስፖርትና ሎጀስቲክስ ሚኒስቴር እና የኢዲአር ማኔጅመንትና የዞኑ ከፍተኛ አመራሮችና ነዋሪዎች በተገኙበት ለዞኑ አስተዳደር የሚያስረክብ እንደሆነ ከኢዲአር የሴፍቲ፣ኢንቫሮመንትና ኳሊቲ ዲፖርትመንት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።