ህዳር 6 ቀን 2016 ዓ.ም (ኢዲአር)፦ ንብረትነታቸው የኢትዮ ጅቡቲ ባቡር አ.ማ የሆኑና በተለያዩ ጊዜያት ተሰርቀው በፖሊስ ጣቢያ በኤግዚቢትነት የተያዙ ከ1ሺህ 3 መቶ በላይ የባቡር መሠረተ ልማት ቁሳቁሶች ወደ ኢዲአር ተመላሽ ተደርገዋል።
ቁሳቁሶቹ ከተጠርጣሪዎች ጋር ተይዘው የፍርድ ሂደቱ እስከሚጠናቀቅ እንዲሁም ከተጠርጣሪ ውጪ የተያዙና በተለያዩ ፖሊስ ጣቢያዎች በኤግዚቢትነት ተመዝግበው የነበሩ መሆናቸው ተመላክቷል።
ከድሬዳዋ አሰተዳደር መልካ ጀብዱ ፖሊስ ጣቢያ ሁለት መቶ ዘጠኝ፣ ከዱከም ፖሊስ ጣቢያ ስምንት መቶ ሃምሳ ሦስት፣ ከሸገር ከተማ ገላን ጉዳ ክፍለ ከተማ ፖሊስ ጣቢያ ሦስት መቶ ሦስት በድምሩ አንድ ሺህ ሦስት መቶ ስድሳ አምስት የተለያዩ የባቡር መሠረተ ልማት ቁሳቁሶች ወደ ድሬዳዋና እንዶዴ ባቡር ጣቢያዎች ንብረት ክፍል ገቢ ሆነዋል።
የኢዲአር የህግ ክፍል ከግዢና ንብረት ክፍል ጋር በመሆን ለረጅም ጊዜ በኤግዚቢትነት ተይዘው የነበሩትን የባቡር ቁሳቁሶች ተመላሽ እንዲሆኑ ከፍተኛውን ሚና ተጫውተዋል።