ህዳር 9 ቀን 2016 ዓ.ም (ኢዲአር)፦ ስምምነቱ የተፈረመው በትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር፣ በኢትዮ-ጅቡቲ ስታንዳርድ ጌጅ ባቡር ትራንስፖርት አክሲዮን ማህበር (ኢዲአር) እና በአዳማ ከተማ ትራንስፖርት ኤጀንሲ መካከል ነው።
የትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ሚንስትር ዴኤታ ክቡር አቶ በርኦ ሀሰን በዚህ ወቅት እንዳሉት የኢትዮ ጅቡቲ ባቡርን ከከተማ ትራንስፖርት ጋር በማቀናጀት ለዜጎች ቀልጣፋና አስተማማኝ አገልግሎት ለመስጠት በከፍተኛ ፍጥነት እየተሰራ ነው ብለዋል። በአዳማ ባቡር ጣቢያ የሚገለገሉ ዜጎች ወደ ከተማ የሚያደርጉትን ጉዞ ከከተማ ትራንስፖርት ሰጪ ተሽከርካሪዎች ጋር ማቀናጀት ጊዜና ወጪን ከመቀነሱ በተጨማሪ በተሳፋሪዎች ላይ የሚደርስን እንግልት በከፍተኛ ሁኔታ የሚቀንስ በመሆኑ ልዩ ትርጉም አለው ብለዋል።
የኢትዮ ጅቡቲ ባቡር ትራንስፖርት ዋና ስራ አስፈፃሚ አብዲ ዘነበ (ዶ/ር) በበኩላቸው ወደ ህብረተሰቡ ይበልጥ በመቅረብ የባቡር ትራንስፖርትን ተደራሽ ለማድረግ እየተሰራ እንደሚገኝ ጠቁመው በድሬዳዋ ባቡር ጣቢያ የተቀናጀ የባቡር ትራንስፖርት ለመስጠት የተጀመረው ስራ ውጤት እያመጣ በመሆኑ በሌሎቹ የባቡር ጣቢያዎችም ተመሳሳይ አገልግሎት ለመሰጠት በትኩረት እየተሰራ እንደሚገኝ ገልፀዋል።
በዚህም የኮንፈረንስ ከተማ የሆነችው አዳማ በርካታ እንግዶችን የምታስተናግድ በመሆኑ ባቡርን ከከተማ ትራንስፖርት ጋር በማቀናጀት ተሳፋሪዎችን ይበልጥ ለማገልገል በማሰብ የቅንጅት ስራው እውን እንዲሆን መደረጉን ጠቁመዋል።
የአዳማ ከተማ ትራንስፖርት ኤጀንሲ ተወካይ አቶ ተስፋዬ ዳዲ የቅንጅት ስራው የተደራጁ የትራንስፖርት አቅራቢ ማህበራትን ይበልጥ ተጠቃሚ የሚያደርግና የህብረተሰቡን እንግልት የሚቀርፍ በመሆኑ ትልቅ ፋይዳ አለው ብለዋል።
በስምምነት መድረኩ የአዳማ ከተማ ብልፅግና ፓርቲ አደረጃጀት ኃላፊ የተከበሩ ወ/ሮ አሚና እንኩሹን ጨምሮ የአዳማ ከተማ ትራፊክ ፖሊስ ሃላፊ፣ የአዳማ ከተማ ልዩ ክፍለ ከተማ አዛዥና የአዳማ ከተማ የትራንስፖርት ማህበራት ተወካይ ተገኝተዋል።