በኢትዮ-ጅቡቲ የባቡር መስመር ደህንነት ዙሪያ ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር ምክክር ተደረገ

በኢትዮ -ጅቡቲ የባቡር መስመር ደህንነት ላይ የሚያጋጥሙ የደህንነት ችግሮችን በመወያየትና የመፍትሄ ሀሳብ ለማቅረብ የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር  ሚኒስትር ድኤታ ክቡር አቶ በርኦ ሀሰን ፣ የኢትዮ -ጅቡቲ ስታንዳርድ ጌጅ የባቡር ትራንስፖርት አክሲዮን ማህበር ዋና ስራ አስፈጻሚ ዶ/ር አብዲ ዘነበ እንዲሁም የክልልና የከተማ ትራንስፖርት ቢሮ ኃላፊዎችና ባለሙያዎች  በተገኙበት በጋራ ምክክር ተደርጓል::

በውይይት መድረኩ ላይ ክቡር አቶ በርኦ ሀሰን  የሃገሪቱን ወጪና ገቢ ንግድ በማቀላጠፍ ረገድ የባቡር ትራንስፖርት አገልግሎት ለአንድ ሃገር ብሎም በባቡር መስመሩ ላይ ለሚገኝ የሕብረተሰብ ክፍሎች የሚያበረክተው አስተዋጽኦ ከፍተኛ መሆኑ ገልፀው  በባቡር መሰረተ-ልማቱና አግልግሎት ላይ በሚያጋጥሙ የደኅንነት ችግሮች የተነሳ መሰረተ-ልማቱ ለሃገራችን ማበርከት የሚገባውን አስተዋጽኦ እንዳያበረክት ከፍተኛ ተግዳሮት እየሆነ ነው ብለዋል፡፡  ሰለሆነም በባቡር ዘርፍ እየተሰተዋሉ ያሉትን ሕገ-ወጥ ተግባራት በመከላከል የባቡር ትራንስፖርት አገልግሎትን ለማሻሻል  በጸጥታው እና በትራንስፖርት ዘርፉ ያሉ አካላት ድርሻ ከፍተኛ በመሆኑ  ይህ የውይይት መድረክ መዘጋጀቱ አሰፈላጊ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

የኢትዮ -ጅቡቲ ስታንዳርድ ጌጅ የባቡር ትራንስፖርት አክሲዮን ማህበር ዋና ስራ አስፈጻሚ ዶ/ር አብዲ  ዘነበ በበኩላቸው ባለፉት አራት ዓመታት በኢትዮ-ጅቡቲ የባቡር ትራንስፖርት ተጨባጭ አወንታዊ እድገት  በጭነትም ሆነ በህዝብ ትራንስፖርት ላይ ማሳየቱን ገልፀው  በተለይ ወደ ሀገር ውስጥ በሚገቡና ወሳኝ በሚባሉ የማዳበሪያ፣ የስንዴ፣ የዘይት አቅርቦት ላይ ባቡሩ ከፍተኛ ድርሻ ነበረው ያሉት ዋና ስራ አሰፈፃሚው በባቡሩ ምልልሰ ላይ የሚያጋጥሙ የውጭም ሆነ የውስጥ  ተግዳሮቶችን በቅንጂት ለመፍታት እንዲህ ዓይነት የምክክር መድርግ ማዘጋጀት ችግሮችን ለመፍታት ትልቅ ድርሻ አለው ብለዋል::

የኢትዮ-ጅቡቲ የባቡር መስመር 756 ኪ.ሜ ርዝመት ሲኖረው 665 ኪ.ሜ. ኢትዮዽያ ውስጥ እና 91 ኪ.ሜ ደግሞ በጅቡቲ የሚገኝ ሲሆን ኢትዮጵያ ውስጥ በ4 ክልሎች ማለትም ኦሮሚያ፣ አማራ፣ አፋር እና ሶማሌ እና በ2 የከተማ መስተዳድሮች አዲስ አበባ እና ድሬዳዋ  ያቋርጣል ተብሏል።

በሁለት አገሮች የሁለትዮሽ ስምምነት የተመሰረተው  የኢትዮ -ጅቡቲ ስታንዳርድ ጌጅ የባቡር ትራንስፖርት አክሲዮን ማህበር ከ2018 (እ.ኤ.አ) ዓ.ም ጀምሮ የጭነት እና የመንገደኛ ትራንስፖርት አገልግሎት እየሰጠ ያለ ሲሆን  በ2021(እ.ኤ.አ)  1.89 ሚሊዮን ቶን ጭነት እና 140,000 መንገደኞችን ያጓጓዘ  ቢሆንም የባቡር የመስመሩ ለአደጋ ተጋላጭነት መጨመር ፣ በመሰረተ ልማቱ ላይ ስርቆትና ውድመት መብዛት፣ ባቡሩን በጉዞ ላይ እያለ  የማገት  ችግሮች  በመኖራቸው የባቡሩ የምልልስ አቅሙ ውስንነት  እና የመለዋወጫ  ወጪ እጥረት በተቋሙ ላይ ማስከተሉ ተገልፃል::

በመጨረሻም በቀረቡ ጉዳዮች ዙሪያ ከባለድርሻ አካላት ጋር አሰተያየትና የመፍትሄ ሀሳብ ከቀረበ በኃላ ክቡር አቶ በርኦ ሀሰን  ችግሩ አንገብጋቢ ችግር በመሆኑን  እና ችግሮችን ሁሉም ክልሎች እና ከተማ መስተዳደሮች ከማህበረሰቡ ጋር ሆነው፤ አደረጃጀትና ግንዛቤ በመፈጠር ችግሮችን መፍታት እንደሚገባቸው እና ሁሉም ባለድርሻ አካላት ችግሮችን ለመፍታት አቅደው እንዲሰሩ እና በቀጣይ ግምገማዎች ላይ በሚሰሩ ስራዎች እውቅናና ተጠያቂነትን እያሰፈኑ መሄድ ያስፈልጋል ብለዋል::

S1
S10
S11
S13
S14
S2
S3
S5
S6
S7
S8
S9